top-news-1350×250-leaderboard-1

ትረምፕ “አሜሪካ ተመልሳለች” አሉ

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትረምፕ ማክሰኞ ምሽት በአሜሪካ የሁለቱ ምክር ቤቶች የጋራ ጉባኤ ላይ ተገኝተው ያደረጉትንን ንግግር “አሜሪካ ተመልሳለች” በማለት የጀመሩት ሲኾን፣ የሪፐብሊካን ሕግ አውጪዎች “ዩ ኤስ ኤ” በሚል ዝማሬ አጅበዋቸዋል።

“ከስድስት ሳምንት በፊት እዚህ ቆሜ የአሜሪካን ወርቃማ ዘመን ዐውጄ” ነበር ያሉት ትራምፕ ከዚያን ጊዜ ወዲህ በሀገራችን ታሪክ ውስጥ ታላቅ እና ስኬታማ ዘመን ለማምጣት ፈጣን እና የማያቋርጥ ተግባራት ተከናውነዋል” ብለዋል።

“አስተዳደራቸው በ43 ቀናት ውስጥ ብቻ ሌሎች ብዙ አስተዳደሮች በአራት እና ስምንት ዓመታት ውስጥ ካከናወኗቸው የበለጠ መሠራቱን” የገለጹት ትረምፕ “ገና እየጀመርን ነው” ብለዋል።

ትረምፕ እስካሁን 76 የፕሬዝደንት ማዘዣዎችን የፈረሙ ሲሆን አብዛኞቹ በፍርድቤት ክስ ተመስርቶባቸዋል።

ትረምፕ ንግግራቸውን ከጀመሩ ከጥቂት ደቂቃ በኋላ በምክር ቤቱ አዳራሽ ከተሰበሰቡ ሰዎች በተሰማ የስላቅ ድምፅ ንግግራቸው በመስተጓጎሉ የተወካዮች ምክርቤቱ አፈ-ጉባኤ ማይክ ጆንሰን የምክርቤቱ ሥነ ስርዐት አስከባሪዎች፣ በቴክሳስ ዲሞክራት ፓርቲን ወክለው ለምክርቤት አባልነት የተመረጡትን አል ግሪን ከምክርቤቱ እንዲያስወጧቸው አዘዋል። ሌሎች የምክር ቤቱ አባላትም ሥነ-ስርዐት እንዲከተሉ አሳስበዋል።

የምክር ቤቱ አባላት

ግሪን ከምክርቤቱ አዳራሽ ከወጡ በኋላ ትረምፕ ንግግራቸውን ቀጥለዋል። ተረምፕ በዚኹ የማክሰኞ ምሽት ንግግራቸው “የመጀመሪያው ወር የፕሬዝደንትነት ዘመኔ፣ በሀገራችን ታሪክ እጅግ ስኬታማው መሆኑን ብዙዎች ገልጸውታል” ያሉት ትራምፕ፣ በድንበር በኩል የሚፈፀም ሕገወጥ ሽግግርን ለማስቆም የወሰዱትን ርምጃም አብራርተዋል።

“በሀገራችን ላይ የሚፈፀመውን ወረራ ለመመከት” በደቡባዊ ድንበር ላይ ብሔራዊ የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ማወጃቸውን እና የዩናይትድ ስቴትስ ጦር በድንበር ላይ እንዲሰፍ ማድረጋቸውንም ገልጸዋል። በዚህም ምክንያት “ባለፈው ወር በሕገወጥ መንገድ ድንበር አያርጠው የሚገቡ ስደተኞች ቁጥር እስከዛሬ ከተመዘገበው ዝቅተኛ ነው” ብለዋል።

በተጨማሪም ወደ ዋይት ሐውስ እንደተመለሱ የፌደራል ቅጥር ሂደቶች እና የውጭ ርዳታዎች ላይ እግድ መጣላቸውን ገልጸዋል። የፌደራል መንግሥት መሥሪያ ቤቶችን ቁጥር እና ሠራተኞችን ለመቀነስ፣ በምፅሃረ ቃሉ ‘ዶጅ’ በመባል የሚጠራ በኢላን መስክ የሚመራ ተቋም መመስረታቸውን የተናገሩት ትረምፕ በቢሊየኖች የሚቆጠር የመንግሥት ገንዘብ እያዳነ መሆኑንም አመልክተዋል።

ትረምፕ በንግግራቸው በዩናይትድ ስቴትስ በ48 ዓመት ውስጥ ያልታየውን የዋጋ ግሽበት ለማስተካከል ከወሰዷቸው ርምጃዎች መካከል “ወርቃማ ፈሳሽ” ሲሉ የጠሩትን የነዳጅ ጋዝ ቁፋሮ እያካሄዱ መሆኑን ተናግረዋል። “የወሳኝ እና ብርቅዬ ማዕድናት” ምርት እንደሚፋጠንም ገልጸዋል።

“ቀጣዩ የግብር ቅነሳ ነው” ያሉት ትራምፕ፣ ከገቢ ግብር፣ ከቲፕ ገንዘብ እና ከትርፍ ሰዓት ክፍያ ላይ ግብር እንደሚያነሱም ተናግረዋል።

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ለሁለቱ ምክር ቤቶች የጋራ ጉባኤ ንግግር ሲያደርጉ
የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ለሁለቱ ምክር ቤቶች የጋራ ጉባኤ ንግግር ሲያደርጉ

ትረምፕ አክለው አሜሪካን “ኢ-ፍትሃዊ” ሲሉ ከገለጹት የፓሪስ የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት፣ “ሙሰኛ” ካሉት የዓለም ጤና ድርጅት እና “ፀረ-አሜሪካዊ” ሲሉ ከገለፁት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት ማስወጣታቸውን አብራርተዋል።

የፕሬዝደንት በዓለ ሲመት ባልተካሄደባቸው ዓመታት “ዘ ስቴት ኦፍ ዘ ዩኒየን” በመባል የሚጠራው እና የአሜሪካ ፕሬዝደንቶች ለጋራ ምክርቤቱ የአሜሪካን አኹናዊ ሁኔታ በሚያብራሩበት በዚህ ንግግር፤ ትራምፕ ለዩናይትድ ስቴትስ ኢኮኖሚ እና ኢሚግሬሽን ፖሊሲ ያላቸውን ርዕይ ለሕዝብ የሚያቀርቡበት እና የፌደራል ሠራተኞችን ቅነሳ እና ከዩክሬን ፕሬዝደንት ጋራ የነበራቸውን እሰጥ አገባ አስመልክቶ የሚያብራሩበት ዕድል ፈጥሮላቸዋል።

ትረምፕ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ከዩክሬኑ ፕሬዝደንት ቮለድሚር ዜለንስኪ ጋራ ያደረጉትን ኃይለቃል የተሞላበት ውይይት ተከትሎ ዩናይትድ ስቴትስ ለዩክሬን የምትሰጠውን ወታደራዊ ርዳታ አቋርጣለች።

“አውሮፓውያን ዩክሬንን ከመደገፍ ይልቅ ከሩስያ ለሚገዙት ነዳጅ እና ዘይት የበለጠ አውጥተዋል” ያሉት ትራምፕ የዩክሬን ፕሬዝደንት ለሰላም ዝግጁ መሆናቸውን የሚገልፅ ደብዳቤ እንደፃፉላቸው አመልክተዋል።

ትረምፕ አክለው “በተመሳሳይ ጊዜ ከሩሲያ ጋራ ጠንከር ያለ ውይይት አድርገን ለሰላም ዝግጁ መኾናቸውን የሚያሳይ ምልክቶች አግኝተናል” ብለዋል።

Crédito: Link de origem

Leave A Reply

Your email address will not be published.