top-news-1350×250-leaderboard-1

የዩክሬን ሩሲያ አስቸኳይ የ30-ቀናት ተኩስ አቁም ተከትሎ የቡድን 7 ሀገራት ይወያያሉ

በኢንዱስትሪ የበለጸጉ የቡድን 7 ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች፣ የሦስት ዓመቱን የሩሲያ ወረራ እየመከተች ላለችው ዩክሬን የሚሰጡትን ድጋፍ ጨምሮ፣ በተለያዩ ጉዳዮች ለበርካታ ቀናት ለመምከር፣ በኩቤክ ካናዳ ይሰበሰባሉ፡፡

ውይይቱ ዩክሬን እና አሜሪካ ከፍተኛ ባለሥልጣናት በሳዑዲ አረቢያ ጂዳ ከተገናኙ በኋላ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ለዩክሬን የምታደርገውን የመረጃ ልውውጥ እና የፀጥታ ድጋፍ እንድምትቀጥል ያሳለፈችውን ውሳኔ ተከትሎ ነው።

ዩክሬን ከሩሲያ ጋራ በሚደረገው ጦርነት “የ30 ቀን አስቸኳይ ጊዜያዊ የተኩስ አቁም” የሚለውን የአሜሪካ ሐሳብ ለመቀበል ዝግጁ መሆኗን ትላንት ማክሰኞ አስታውቃለች።

የጀርመኑ መሪ ቻንስለር ኦላፍ ሾልዝ ትላንት ረቡዕ ኤክስ በተሰኘ ገጻቸው እንደተናገሩት “ለዩክሬን ፍትሃዊ ሰላም ወሳኝ እና ትክክለኛ ርምጃ ነው” በማለት የ30 ቀን የተኩስ አቁም ሐሳብን ተቀብለዋል።

የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ዩክሬን ሐሳቡን መቀበሏ ሩሲያ እንድትስማማ ጫና ይፈጥራል ብለዋል።

ሩቢዮ አያይዘውም “አሁን ይህን ጥያቄ ከተስፋ ጋራ ወደ ሩሲያውያን እንወስዳለን፣ እሺ እንደሚሉም ተስፋ እናደርጋለን፡፡ ለሰላም እሺ ይላሉ፡፡ ኳሱ አሁን በእነሱ ሜዳ ውስጥ ነው” ብለዋል፡፡

በጂዳ ከሩቢዮ ጋራ የነበሩት የአሜሪካ ብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ማይክ ዎልትስ፣ በተኩስ አቁም ስምምነቱ ላይ ለመወያየት፣ በቅርቡ ከሩሲያ አቻቸው ጋራ ለመነጋገር አቅደዋል፡፡

ነገ ሐሙስ የኔቶ ዋና ጸሃፊ ማርክ ሩት፣ ዋይት ሐውስን ይጎበኛሉ።

እነዚህ ሁሉ ውይይቶች የሰላሙን ሂደት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የሚደረገው ጥረት አካል መሆናቸው ተገልጿል።

የዩክሬን ፕሬዝደንት ቮሎዲሚር ዜለንስኪ በአሜሪካ እና ዩክሬን ድርድር ላይ አልተሳተፉም፡፡ ይሁን እንጂ ትላንት ማክሰኞ ምሽት ባደረጉት ንግግር የተኩስ አቁም እቅዱ “አዎንታዊ ጥያቄ” ነው ብለዋል።

ዜለነስኪ አክለውም “አሁን ሩሲያ ተመሳሳይ ነገር እንድታደርግ ማሳመን የዩናይትድ ስቴትስ ጉዳይ ነው” ብለዋል።

ሩሲያ ከተስማማች የተኩስ አቁም ስምምነቱ ወዲያውኑ ተግባራዊ ይሆናል።

ትረምፕ ለቀጣይ ወታደራዊ ርዳታ የዩክሬንን ጥሬ ዕቃ ማግኘትን እንደ ቅድመ ሁኔታ በማስቀመጥ ፍላጎት አሳይተዋል።

የማክሰኞውን ድርድር ተከትሎ ሁለቱም ወገኖች “የዩክሬንን ኢኮኖሚ ለማስፋፋት እና የዩክሬንን የረዥም ጊዜ ብልጽግና እና ደኅንነትን ለማረጋገጥ፣ እንዲሁም የዩክሬንን ወሳኝ የማዕድን ሀብት ለማልማት በተቻለ ፍጥነት ሁሉን አቀፍ ስምምነት ለማድረግ መስማማታቸውን ያወጡት የጋራ መግለጫ ያስረዳል፡፡

Crédito: Link de origem

Leave A Reply

Your email address will not be published.