በሰሜን ጎንደር ዞን ደባርቅ ወረዳ፣ ከትላንት በስቲያ ማክሰኞ በደረሰ የመኪና አደጋ የ16 ሰዎች ሕይወት ማለፉን፣ የሰሜን ጎንደር ዞን ፖሊስ መምሪያ አስታወቀ።
በዐማራ ክልል የሰሜን ጎንደር ዞን ፖሊስ መምሪያ የትራፊክ ትምህርት እና ሥልጠና ክፍል ሓላፊ ኢንስፔክተር ይበልጣል መርሻ፣ ዛሬ ኀሙስ ለአሜሪካ ድምፅ በስልክ እንደገለጹት፣ ከትላንት በስቲያ ኀሙስ፣ የካቲት 18 ቀን 2017 ዓ.ም. ከረፋዱ 3:30 ገደማ፣ የሰሌዳ ቁጥሩ ኢት-11591 የኾነ፣ በተለምዶ ካሶኒ እየተባለ የሚጠራ የደረቅ ጭነት መኪና፣ ከበየዳ ወደ ደባርቅ ከተማ ሰዎችንና እህል ጭኖ እየተጓዘ ሳለ፣ ልዩ ስሙ አበርጊና በተባለው ስፍራ ላይ በመገልበጡ 16 ተሳፋሪዎች ሲሞቱ፣ በ35ቱ ላይ ቀላል እና ከባድ የመቁሰል አደጋ ደርሷል።
ከ16ቱ ሟቾች መካከል አራቱ ተፈናቃዮች ናቸው፤ ያሉት ኢንስፔክተር ይበልጣል፣ የጭነት መኪናው አሽከርካሪ እስከ አኹን በቁጥጥር ሥር እንዳልዋለ ተናግረዋል።
ከአደጋው ከተረፉት ተሳፋሪዎች አንዱ እንደኾነ የሚናገረው ዮሐንስ ምትኬ፣ በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ሳቢያ ከትግራይ ክልል በ2013 ዓ.ም. ተፈናቅሎ በደባርቅ ወረዳ ከማኅበረሰቡ ጋራ ተቀላቅሎ እንደሚኖር ጠቅሶ፣ ወደ በረሓ ለሥራ ፍለጋ እየተጓዘ እንደነበር ገልጿል። ለዚኽም፣ ከአበርጊና ቀበሌ ከእርሱ ጋራ 18 ተፈናቃዮች በተሽከርካሪው መሳፈራቸውን አውስቶ፣ አንድ ኪሎ ሜትር እንኳን ሳይርቅ አደጋው መድረሱን አስረድቷል።
ዮሐንስ አደጋው በእጁ ላይ ባደረሰበት ጉዳት፣ በደባርቅ ሆስፒታል በሕክምና እየተረዳ እንደሚገኝ አስታውቆ፣ አብረውት ከተሳፈሩት ውስጥ ሕይወታቸው ያለፈ እንዳሉም ገልጿል።
በቅርቡ የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ምክንያት ከትግራይ ክልል ተፈናቅለው በደባርቅ ወረዳ ከማኅበረሰቡ ጋራ ተቀላቅለው ከሚኖሩት መካከል የተፈናቃዮች ማኅበር ምክትል ሊቀ መንበር የኾኑት መሪጌታ ጠበቃው ወልደ ገብርኤል፣ ከ2015 ዓ.ም. ወዲህ በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ ርዳታ ስለሚሰጣቸው አብዛኛዎቹ ለቀን ሥራ ከቦታ ወደ ቦታ እንደሚንቀሳቀሱ ገልጸዋል።
ከትላንት በስቲያው የመኪና አደጋ ጉዳት የደረሰባቸው 18 ተፈናቃዮች ግን፣ የዓለም ባንክ በአበርጊና ብር እና ምግብ ይሰጣል፤ ለሥራ ያደራጃል፤ የሚል መረጃ ሰምተው እንደተጓዙና በስፍራው ከደረሱ በኋላ ግን ርዳታ እንደማይሰጥ ሲረዱ ለሥራ ፍለጋ ወደ በረሓ ለመሔድ ዐቅደው እየተመለሱ እንደነበር፣ የማኅበሩ ምክትል ሊቀ መንበር መሪጌታ ጠበቃው አብራርተዋል።
በደባርቅ ወረዳ፣ ከሁለት ሺሕ በላይ የጦርነት ተፈናቃዮች ከማኅበረሰቡ ጋራ ተቀላቅለው ይኖራሉ።
Crédito: Link de origem