top-news-1350×250-leaderboard-1

በሚያንማር በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ 32 ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው ተመለሱ

በሚያናማር በእገታ ሥር ቆይተው ወደ ታይላንድ ከተሻገሩ 133 ኢትዮጵያ መካከል 32ቱ ዛሬ ወደ አገራቸው መመለሳቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገልጿል።

በዛሬው ዕለት ከገቡት መካከል አስተያየቱን የሰጠን አንድ ወጣት፣ በምያንማር ለዐሥር ወራት አስከፊ ጊዜ ማሳለፉን ተናግሯል።

ደርሶብኛል ካላቸው አካላዊ የመብት ጥሰቶች በተጨማሪ፣ በሥነ ልቡና ክፉኛ በመጎዳቱ ምክንያት ስሙ እንዳይጠቀስ የጠየቀን ወጣቱ፣ ምንም እንኳን የእርሱ ወደ አገሩ መግባት ቢያስደስተውም፣ ነገር ግን ደስታው ምሉዕ እንዳለሆነ ይገልጻል፡

ከሚያንማር ወደ ታይላንድ የመግባት ዕድል ካገኙት 138 ኢትዮጵያውያን ውስጥ አምስቱ ከዚህ ቀደም ለብዙኅን መገናኛ በሰጡት አስተያየት ምክንያት በሚያንማር ኢሚግሬሽን ትፈለጋላችሁ ተብለው መወሰዳቸውን ከተመላሾቹ መካከል ያነጋገርነው ወጣት አመልክቷል፡፡ እነርሱን ጨምሮ መንግሥት፣ በታይላንድ በካምፕ ውስጥ የሚገኙትን እና በሚያንማር በችግር ላይ ያሉትን ኢትዮጵያውያን ለመታደግ “ከፍተኛ ጥረት ሊያደርግ ይገባል” ሲል ተማፅኗል፡፡

በጉዳዩ ላይ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስተያየት ለማግኘት ያደረግነው ጥረት፣ የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር ነቢያት ጌታቸው የእጅ ስልክ ላይ ደውለን ባለመመለሳቸው ለአሁን አልተሳካም፡፡

ሆኖም፣ በዛሬው መገልጫው “43 ኢትዮጵያውያን ዛሬ ምሽት ወደ አገር ቤት ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል” ያለው ሚኒስቴሩ፣ ቀሪዎቹን በታይላንድ ማቆያ የሚገኙ 58 ኢትዮጵያውያንን ወደ አገራቸው ለመመለስም በሕንድ ያለው የኢትዮጵያ ኤምባሲው ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ ገልጿል፡፡

በማይናማር በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ሌሎች ኢትዮጵያውያንን ወደ ታይላንድ በማሻገር ወደ አገራቸው ለመመለስ ደግሞ፣ ጃፓን በሚገኘውን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጥረት እያደረገ ነው ብሏል፡፡

በታይላንድ ጥሩ ክፍያ የሚያስገኝ ሥራ ትቀጠራላችሁ በሚል፣ በሕገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ተታለው በተለያዩ ጊዜያት ወደ አገሪቱ ከሄዱ በኋላ ማረፊያቸው ሚያንማር

የኾነ ኢትዮጵያውያን ቁጥር በይፋ ባይታወቅም በሺሕዎች እንደሚቆጠር ከተለያዩ ምንጮች የሚገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

ከነዚህም አብዛኛው፣ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ማጭበርበር (ስካሚንግ) ወንጀል በሚፈጽሙ በሕገወጥ የተደራጁ ቡድኖች ቁጥር ስር ሆነው፣ በአስገዳጅ ሁኔታ በዚሁ ተግባር ላይ እንዲሰማሩ የተደረጉ ናቸው፡፡

Crédito: Link de origem

Leave A Reply

Your email address will not be published.