ከቻይና የሚሳይል ነዳጅ መስሪያ ቁልፍ ግብአቶችን ጭናለች ተብላ በምዕራባዊያን የዜና ዘገባዎች የተጠረጠረችው ሁለተኛዋ የኢራን መርከብ ወደ ኢራን እያመራች መሆኑን የቪኦኤ ልዩ የትንታኔ ዘገባ አመልክቷል፡፡
የመርከብ እንቅስቃሴ ክትትል ድረ-ገጾች እንደሚያሳዩት የኢራን ባንዲራ የሚያውለበልበው ጃይራን የተባለው የጭነት መርከብ፣ ከቻይና ይነሳል ተብሎ ከተጠበቀበት ጊዜ ከአንድ ወር በኋላ ዘግይቶ ባለፈው ሰኞ መነሳቱ ተጠቅሷል፡፡
በጥር እና በየካቲት ዘ ፋይናንሺያል ታይምስ፣ ዘ ዎል ስትሪት ጆርናል እና ሲ ኤን ኤን ባቀረቧቸው ዘገባዎች፣ ቴህራን በሚሳይል ነዳጅ ውስጥ ጥቅም ላይ የሚውለውን 1,000 ሜትሪክ ቶን ኬሚካል (ሶዲየም ፐርክሎሬት) ለመጫን ከምትጠቀምባቸው ሁለት መርከቦች መካከል ጃይራን አንዱ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡
ሦስቱ የዜና ማሰራጫዎች ስማቸው ያልተጠቀሱ የምዕራባውያን የስለላ ምንጮችን ጠቅሰው እንደተናገሩት የተጠቀሱት ኬሚካሎች ለኢራን 260 መካከለኛ ርቀት ሚሳይሎችን ማምረት ያስችላሉ፡፡
በዘገባዎቹ ጎልቦን በሚል ስያሜ የተጠቀሰው ሌላኛው የኢራን የጭነት መርከብ፣ እ ኤ አ የካቲት 13 ከምሥራቃዊ ቻይና ብሩክ አባስ ወደተባለው የኢራን ወደብ ያደረገውን የ19 ቀናት ጉዞ አጠናቋል፡፡
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የጃይራን ከቻይና መነሳት አስመልክቶ ከቪኦኤ ለቀረበለት ጥያቄ ምንም አስተያየት አልሰጠም፡፡ በኒውዮርክ የሚገኘው የኢራን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሚሽንም ባለፈው ማክሰኞ በኢሜል ለተላከከለት ተመሳሳይ የቪኦኤ ጥያቄ ምላሽ አልሰጠም።
ባለፈው ወር የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለቪኦኤ እንደተናገረው፣ ኢራን ኬሚካሎቹን ለማስመጣት፣ ጎልቦን እና ጃይራን የተባሉ መርከቦችን እንደምትጠቀም በፋይናንሺያል ታይምስ እና ዎል ስትሪት ጆርናል ከወጡ ዘገባዎች ተመልክቷል፡፡
ቃል አቀባዩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በደህንነት መረጃ ጉዳዮች ላይ ምንም ዐይነት አስተያየት ባይሰጥም “ለኢራን ሚሳይል ወይም ሌሎች የጦር መሳሪያ ፕሮግራሞች ሊጠቅሙ የሚችሉ እቃዎች፣ መሣሪያዎች እና ቴክኖሎጂዎች መስፋፋትን መከላከል ላይ ማትኮሩን እና ኢራንን በማዕቀብ ተጠያቂ ማድረጉን ቀጥሏል” ብለዋል ።
የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ፣ ማኦ ኒንግ፣ እ ኤ አ ጥር 23 በዜና ማሰራጫዎቹ ስለቀረቡት ዘገባዎች በሰጡት ምላሽ ፣ ቻይና፣ በራሷ የኤክስፖርት ቁጥጥር እና፣ በዓለም አቀፍ ግዴታዎች እንደምትገዛ ጠቅሰው፣ እንደ ህገ ወጥ የተናጠል ማዕቀቦች የምትቆጥራቸውን የሌሎችን ሀገሮች ተጽዕኖ እንደማትቀበል ተናግረዋል፡፡
ባለፈው ወር የቻይና መንግሥት የመገናኛ ብዙሃን ስለ ጃይራን ጉዞ ምንም ተናግረው አያውቁም፡፡ በቻይና ማህበራዊ ሚዲያ መድረኮችም ስለ ኢራን መርከብ የተደረገ ውይይት እንዳልነበረ የቪኦኤ የማንዳሪን ቋንቋ አገልግሎት ዘገባ አመልክቷል፡፡
መሠረቱን ኒው ዮርክ ያደረገ ፣ የፖለቲካዊ ስጋቶች ጉዳይ አማካሪ ተቋም፣ ዩሬዥያ ቡድን ከፍተኛ የኢራን ተንታኝ የሆኑት፣ ግሪጎሪ ብሩው፣ “ኢራን፣ ጃይራንን ከመላኳ በፊት፣ ጎልቦን የተባለው ሌላኛው መርከብ ጉዞውን ክልከላ ሳይገጥመው ለማጠናቀቅ ይችል እንደሆነ ለመፈተሽ ፈልጋ ሊሆን ይችላል” ብለዋል ።
ብሩው አያይዘውም “በአሜሪካ ማዕቀብ ሥር ከሆነው የኢራን ሚሳይል ኢንዱስትሪ ጋር የተያያዙ በጣም ሚስጥራዊነት ያላቸው ቁሶችን የያዙ መርከቦች የመያዝ አደጋ ተጋርጦባቸዋል፣ ኢራናውያንም ይህን አውቀውታል” ብለዋል ።
በጂም ሪሽ እና በፒት ሪኬትስ የሚመሩ ስምንት ሪፐብሊካን ሴነተሮች፣ እ ኤ አ የካቲት 4 ቀን ስለ ኢራን-ቻይና የኬሚካል ትብብር ደባ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ደብዳቤ ልከዋል፡፡
የዜና ማሰራጫዎቹ ዘገባዎች ትክክለኛ ከሆኑ ከአሜሪካ ዓለም አቀፍ አጋሮች ጋር በመተባበር “አሁን ጉዞ ላይ የሚገኘውን ጭነት ጣልቃ ገብተው እንዲያስቆሙ” አሳስበዋል ።
በቅርቡ ጎልቦን ከቻይና ወደ ኢራን ባደረገው ጉዞ መንገድ ላይ መያዙን የሚያሳይ ምንም ምልክት አልታየም።
የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ስለ ደብዳቤው ከቪኦኤ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፡- “ከምክር ቤት ጋር በሚደረጉ መልእክቶች ላይ አስተያየት አንሰጥም” ብለዋል።
የሪኬትስ ቢሮም ሩቢዮ ከሴነተሮቹ ለተላከላቸው ደብዳቤ ምላሽ ሰጥተው እንደሆነ ከቪኦኤ ለቀረበለት ጥያቄ ምላሽ አልሰጠም።
Crédito: Link de origem