top-news-1350×250-leaderboard-1

የዛሬው የግሪንላንድ ምርጫ ነጻ አገር የመሆን ምኞቶች የሚፈተሹበት ነው ተባለ

የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ በማዕድን የበለጸገችውን ደሴት ለመቆጣጠር ፍላጎት እንዳላቸው ያንጸባረቁበት ውጥን ዓለም አቀፍ ትኩረት በሳበበት በዚህ ወቅት ፤ የግሪንላንድ ነዋሪዎች ዛሬ ማክሰኞ ምርጫ እያካሄዱ ነው።

ትረምፕ ሥልጣን እንደተረከቡ ነበር ‘ለዩናይትድ ስቴትስ የደህንነት ጥቅም አስፈላጊ ናት’ ሲሉ ከፊል ራስ ገዟን የዴንማርክ ግዛት የዩናይትድ ስቴትስ አካል ለማድረግ ያላቸውን ፍላጎት ይፋ ያደረጉት።

57, 000 ሕዝብ ብቻ ያላት ደሴቲቱ ግዛት የከበባት በረዶ አለት መቅለጥ የተፈጥሮ ሃብቷን ይበልጥ ተደራሽ እያደረገ በመጣበት እና አዳዲስ የመርከቦች መመላለሻ መንገዶች እየተከፈቱ ባለበት፤ የአርክቲክ ውቅያኖስን እና አካባቢውን በበላይነት ለመቆጣጠር የተያዘው እሽቅድምድም ሆናለች። ሩስያ እና ቻይናም በአካባቢው ወታደራዊ እንቅስቃሴያቸውን አጠናክረው ቀጥለዋል።

ግሪንላንድ እንደ አውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር በ1979 የመጀመሪያው ፓርላማዋ ሲቋቋም የተወሰነ የራስ ገዝ አስተዳደር ስልጣን ተጎናጽፋለች።

ይሁን እንጂ የውጭ ግንኙነቷን፣ እንዲሁም መከላከያ እና የገንዘብ ፖሊሲዋን የሚቆጣጠረው የዴንማርክ መንግሥት ነው። ለኢኮኖሚዋ የሚመደበውም ወጭ በዓመት ከአንድ ቢሊዮን ዶላር ያነሰ ነው።

ከዴንማርክ ተገንጥላ ሙሉ ነፃ ሃገር ለመሆን በሕዝበ ውሳኔ የማወጅ መብት እንደ አውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር በ2009 ብትጎናጸፍም፤ ያለ ዴንማርክ ኢኮኖሚያዊ ድጋፍ የዜጎቿ የኑሮ ደረጃ ሊወድቅ ይችላል በሚል ሥጋት ዕውን ሳታደርገው ቀርታለች።

ይሁን እንጂ ትራምፕ ‘አሳካዋለሁ’ ሲሉ እያራመዱ ያሉት ፍላጎት፣ የአገሬው ተወላጆች ‘ኢኒዩት’ በተሰኘው ጥንታዊ ባህላቸው ያላቸው ኩራት እያደገ ከመምጣቱ ጋር ተዳምሮ፣ ነፃ አገር መሆን የሚለው ሃሳብ በዘንድሮው ምርጫ ልዩ ትኩረት አግኝቷል።

የምርጫ ጣቢያዎች ለ11 ሰዓታት ክፍት ሲሆኑ፤ ውጤቱም በነገው ዕለት ይፋ ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል። ከወዲሁ የሚወጣ የምርጫ ውጤት ትንበያ አይኖርም።

ቀድሞ የዴንማርክ ቅኝ ግዛት እና እንደ አውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር ከ1953 አንስቶ ደግሞ የግዛቷ አካል የሆነችው ግሪንላንድ፡ በቆዳ ስፋቷ ከዩናይትድ ስቴትሷ የቴክሳስ ክፍለ ግዛት በሦስት እጅ ትበልጣለች።

በጥር ወር የወጣ የሕዝብ አስተያየት ግምገማ እንደሚያሳየው አብዛኛው የግሪንላንድ ሕዝብ ግዛቲቱ ነጻ ሀገር እንድትሆን የሚፈልግ ሲሆን ክፍፍል ያለው “መቼ ይሁን እና የሕዝቡ የኑሮ ደረጃ እንዲያሽቆለቁል ካደረገስ?” በሚሉት ጉዳዮች ነው።

Crédito: Link de origem

Leave A Reply

Your email address will not be published.