top-news-1350×250-leaderboard-1

ትረምፕ በመጀመሪያው የምክር ቤት ንግግራቸው ትኩረት ያደርጉባቸዋል የተባሉ ጉዳዮች

በዩክሬን እና በመካከለኛው ምስራቅ በመካሔድ ላይ ያሉትን ጦርነቶች የማስቆም አስፈላጊነት፤ ዩናይትድ ስቴትስ በአገሮች ላይ ቀረጥ መጣሏ እና በሀገር ውስጥ የፌዴራል መንግሥቱን ሠራተኛ ቁጥር መቀነስ፤ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትረምፕ በሁለተኛ የሥልጣን ዘመናቸው የመጀመሪያቸው በኾነው በያዝነው ሳምንት ለምክር ቤቱ በሚያሰሙት ንግግራቸው ትኩረት ያደርጉባቸዋል ተብለው ከሚጠበቁት ጉዳዮች ጥቂቶቹ ናቸው።

የአሜሪካ ድምጿ ቬሮኒካ ባልደራስ ኢግሌሲያስ ያጠናቀረችውን ዘገባ ከተያያዘው ፋይል ይከታተሉ።

የዩናይትድ ስትቴሱ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ እንደ አውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር በ2017 እንዳደረጉት የሁለቱ ምክር ቤቶች አባላት በጣምራ በሚታደሙበት ሥነ ስርዐት ላይ በነገው ዕለት ለሚያሰሙት ንግግር ቀጠሮ ተይዟል።

በሩስያ እና በዩክሬን መካከል እየተካሄደ ያለውን ጦርነት አስመልክቶ፣ በግጭቱ ውስጥ ባሉት ወገኖች መካከል በሚደረገው የሰላም ድርድር አስተዳደራቸው እያደረገ ስላለው ጥረት ትራምፕ በንግግራቸው ልዩ ትኩረት ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የዩናይትድ ስቴትሱ መሪ በእስራኤል-ሐማስ ጦርነት እና በጋዛ የወደፊት ዕጣ ዙሪያ ያላቸውን አቋም አስመልክቶም ለምክር ቤቱ ያሳውቁ ይሆናል ተብሎ ይታመናል።

ትረምፕ እንደ አውሮፓውያኑ የቀን አቆጣጠር ባለፈው የካቲት ወር መጀመሪያ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር ቢኒያሚን ኔታንያሁ ዋሽንግተንን በጎበኙበት ወቅት የጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጡ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ጋዛን እንደ እርሳቸውም ቃል ወደ “መካከለኛው ምሥራቅ ውብ የባሕር ዳርቻ መዝናኛነት” ትቀይራለች የሚል አስተያየት አሰምተዋል።

“ዩናይትድ ስቴትስ ያን ሥፍራ በባለቤትነት በመያዝ፤ ድንቅ እና በሺዎች የሚሰላ የሥራ ዕድል የሚያስገኝ ሁኔታ ትፈጥራለች።”

ትረምፕ በካፒቶል በሚሰሙት በዚህ ንግግራቸው፣ ዩናይትድ ስቴትስ በሌሎች አገሮች ላይ ቀረጥ ስለጣለችባቸው ምክንያቶችም ይናገራሉ ብለው ተንታኞች ይገምታሉ።

ትራምፕ በተጨማሪም አስተዳደራቸው የፌደራል መንግሥቱን ወጪ ለመቀነስ፣ የማጭበርበር ድርጊቶች እና ብክነትን ለመቀነስ በሚል የፌዴራል የሠራተኛ ቁጥርን ለመቀነስ እየወሰደ ባለው ርምጃ ፍጥነት እና መጠን ዙሪያ የሚሰነዘሩ ትችቶችን ይከላከላሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የቀድሞ የዩናይትድ ስቴትስ የደኅንነት መሥሪያ ቤት ባለሞያ የነበሩት የዩናይትድ ስቴትስ እንደራሴዎች ምክር ቤት አባሏ ሴናተር ኤሊሳ ስሎኪን የፕሬዝደንት ትረምፕን ንግግር ተከትሎ የሚቀርበውን የዲሞክራት ፓርቲውን ምላሽ እንዲያሰሙ ተመርጠዋል።

Crédito: Link de origem

Leave A Reply

Your email address will not be published.