top-news-1350×250-leaderboard-1

ከሚያንማር የወንጀል ማዕከሎች የተለቀቁትን ሰዎች በፍጥነት ወደሀገራቸው ለመላክ እንዳልተቻለ ተገለጸ

በታይላንድ እና ሚያንማር ድንበር ላይ በኢንተርኔት አማካይነት የማጨበርበር ተግባር ይፈጽማሉ ከተባሉ ማዕከሎች፣ በታይላንድ፣ቻይና እና ሚያንማር መንግሥታት ትብብር በተወሰደ ርምጃ በግዳጅ ተይዘው የነበሩ በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ሰዎችን ማስለቀቅ ተችሏል።

ከሠላሳ የሚበልጡ አገር ተወላጆች ከተያዙበት የተለቀቁ ሲኾን፣ አኹን ደግሞ ወደየ ሀገራቸው የመመለሱ ኺደት እጅግ ፈታኝ እንደኾነ የካረን የድንበር ጥበቃ ኃይል የተባለው ቡድን ቃል አቀባይ ተናግረዋል።

ከአንድ ሳምንት በፊት የሚያንማር ወታደራዊ ሁንታ አጋር የኾነው ታጣቂ ኃይል፣ ሚያንማርና ታይላንድ ወሰን አቅራቢያ በሚገኘው “ሹዎ ኮኮ” የተባለው አጭበርባሪ መረብ ሥር ከሚሠሩ ማዕከሎች ከ6 ሺሕ የሚበልጡ ሰዎችን በማስለቀቅ ቁልፍ ሚና ተጫውቷል።

የድንበር ጥበቃ ቡድኑ ቃል አቀባይ ሌተና ኮሎኔል ናይንግ ሙዋንግ ዛው ፣ ለአሜሪካ ድምጽ የበርማ ቋንቋ አገልግሎት በሰጡት ቃል በርካታ ሰዎች የተለቀቁ ቢሆንም ወደየ ሀገራቸው የመላኩ ኺደት የተወሳሰበ እና የተጓተተ መኾኑን አስረድተዋል።

“መጀመሪያ በቀን 1ሺሕ ሰዎች ለመላክ አቅደን ነበር። አሁን ግን በአንዴ ለመላክ የቻልነው ጥቂት መቶ ብቻ ነው” ሲሉ ኮሎኔሉ አስረድተዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንዳስታወቀው የተደራጁ የወንጀል ቡድኖች በሺሕዎች የተቆጠሩ ሰዎችን በሕገወጥ መንገድ በማስተላለፍ በተለያዩ የደቡብ ምሥራቅ እስያ ሀገሮች ሚያንማር ያለውን በመሳሰሉ የወንጀል ማዕከሎች ውስጥ በግዴታ ያሠሯቸዋል።

በሺሕዎች የተቆጠሩ ከወንጀለኞቹ እጅ የተለቀቁ ሰዎች የሚያንማር መንግሥት የጉዞ ሂደታቸውን እስከሚያከናውን በጊዚያዊ መጠለያዎች ሆነው በመጠባበቅ ላይ ናቸው።

የካረን ቡድኑ ቃል አቀባይ ለቪኦኤ ሲናገሩ 500 ሰዎች አነስተኛ መጋዘኖች ውስጥ ተጨናንቀው ስለሚኖሩ የበሽታ መቀስቀስ እና የማምለጥ ሙከራ ያጋጥማል የሚል ስጋት መኖሩን አመልክተዋል።

ከወንጀል ማዕከሎቹ ከተለቀቁት ውስጥ በዋናነት በርካታ ቻይናውያን ኢንዶኒዢያውያን የሚገኙበት ሲኾን የኢትዮጵያ፣ ዩጋንዳ፣ኬኒያ፣ሩዋንዳ እና ጋናም ብዙ ዜጎች ካሏቸው 15 ሀገራት መካከል ተጠቅሰዋል።

የታይላንድ መንግሥት ሰዎቹን ደኅነታቸው ተጠብቆ ወደየሀገራቸው ለመመለስ ከሚያንማር እና ከሌሎችም አገሮች ጋራ በቅርበት እየሠራ መሆኑን አስታውቋል።

የወንጀል መረቦቹን የመበጣጠስ ዘመቻው መቀጠሉን የጠቆሙት የሚያንማሩ የድንበር ጥበቃ ብርጌድ ቃል አቀባይ ሆኖም ዘመቻው በቅርቡ እንደሚቋረጥ ገልጸዋል፥ “አሁንም በ10 ሺሕዎች የተቆጠሩ በወንጀለኛ ቡድኖቹ እጅ እንዳሉ እንገምታለን” ያሉት ኮሎኔሉ ሁሉንም አስለቅቆ ወደሀገራቸው የመመለሱ ኾደት ወራት እንደሚፈጅ ገልጸዋል።

Crédito: Link de origem

Leave A Reply

Your email address will not be published.